አቶ ደመቀ መኮንን በሀገር ውስጥና በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከምንጊዜውም በተለየ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባቸው ገለጹ

አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ (ኤ ኤም ኤን) ሚያዚያ 24/2014 ዓ.ም

ብሄራዊ ጥቅማችንን ለማስከበር፣ የአገራችንን ተደማጭነት ለማጠናከርና ተደራሽነታችንን ለማስፋት በሀገር ውስጥና በውጪ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ከምንጊዜውም በተለየ ርብርብ ማድረግ ይገባቸዋል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡


አቶ ደመቀ ዲፌንድ ኢትዮጵያ የአውሮፓ ግብረሀይል የተመሰረተበትን አንደኛ ዓመት ባከበረበት ወቅት በክብር እንድግነት ተገኝተው እንደተናገሩት፤ በተለያየ መልኩ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር ጥረት በሚደረግበት ወቅት ዲፌንድ ኢትዮጵያን የመሳሰሉ የዳያስፖራ አደረጃጀቶች መፈጠራቸው የኢትዮጵያን ድምጽ ለማሰማት ወሳኝ ሚና በመጫወት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር እያከናወናቸው ስላሉ የፐብሊክ ዲፕሎማሲና የሀብት ማሰባሰብ ተግባራት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ዲፌንድ ኢትዮጵያ ከዕድሜው አንጻር ያከናወናቸው ተግባራት አበረታች መሆናቸውን አንስተው፣ በቀጣይም ለበለጠ ተልዕኮና ሃላፊነት እንደሚንቀሳቀስ ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ላይ የተዛባና ያልተጣራ መረጃ ይዘው የተደናገሩትን እውነተኛውን መረጃ በተቀናጀ መልኩ በማቅረብ እውነታውን እንዲረዱ በማድረግ ሀገራችን በሁሉም ማእዘናት ተደማጭ ሆና የምትቀጥልበትና ኢትዮጵያን የሚመጥን ቁመና ይዛ እንድተሻገር ማድረግ ይገባናል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወዳጅ የሆኑትን የበለጠ ማጽናት በተሳሳተ መረጃ ያልተገባ እይታ ያላቸውን እውነታውን እንዲረዱ ከፍተኛ ጥረት ማድረግና ሆን ብለው የሚያደናግሩትን ተጽእኖቸውን በመቀነስ ወደእውነታው መመለስ ዋናው ትኩረታችን ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

በእንግሊዝ የኢትዮጵያ መንግስት ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተፈሪ መለስ በበኩላቸው፤ መንግስትና ዜጎች በተቀናጀ መንገድ የወሰዱት ተደጋጋሚና ተከታታይ እርምጃዎች የተነሳ የተሳሳተ መረጃ ይዘው የነበሩ አንዳንድ ሀገራት ወደእውነታው እየተመለሱ ቢሆንም ይህ እንዳይሳካ እየተረባረቡ ያሉ አካላት ጥረታቸው እንዲከሽፍ የጀመርነውን የዲጂታል ዲፕሎማሲ ከምንጊዜውም በላይ አጠናክረን ልንቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡

ድፌንድ ኢትዮጵያ የአውሮፓ ግበረሀይል የኢትዮጵያን ዕውነት ለዓለም ለማስረዳት የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል የጠየቁ ሲሆን ግብረሀይሉ ባለፉት ጊዜያት ስላደረገው ከፍተኛ ጥረት ምስጋና አቅርበዋል ፡፡

በብራስልስ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሂሩት ዘመነ በበኩላቸው፤ በሽግግር ላይ ያለን ሀገር በመሆናችን በማንኛውም ሂደት ትልቁን የኢትዮጵያን ምስል ማየት እንደሚገባ ገልጸው በአውሮፓ ኅብረት ያለንን ገጽታ የጀመርነውን የዲጂታል ዲፐሎማሲ በጋራና በቅንጅት ከምንጊዜውም በላይ አጠናክረን በመቀጠል የሀገራችንን እውነታ ማስረዳት ይኖርብናል ብለዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሐመድ እንድርስም፤ ዲፌንድ ኢትዮጵያ ባከናወናቸው ፋና ወጊ ተግባራት የኢትዮጵያን የዲጂታል ዲፕሎማሲ ውክልና ማሳደጉን አንስተው፣ የተቋቋመበትን ተግባር ከማከናወን ባለፈ ተቋሙ ራሱን በልዩ ልዩ የአውሮፓ ሀገራት ማስፋፋት መቻሉ የሚበረታታና ሌሎችም የዳያስፖራ አደረጃጀቶች በተሞክሮነት ሊከተሉት የሚገባ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የመሰል አደረጃጀቶች አላማ በዘላቂነት የኢትዮጵያን ጥቅሞች ማስከበርና መከላከል መሆኑን ጠቅሰው፣ ዲፌንድ ኢትዮጵያ የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች ለመደገፍ አገልግሎቱ ሁልጊዜም ዝግጁ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የዲፌንድ ኢትዮጵያ የአውሮፓ ግብረ ሀይል ሊቀመንበር አቶ ዘላለም ጌታሁንም በበኩላቸው፤ ዲፌንድ ኢትዮጵያ በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በለንደን መቋቋሙን አንስተው፣ በሂደትም በ12 የአውሮፓ ሀገራት በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ ገልጽዋል፡፡

ዲፌንድ ኢትዮጵያ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮም የኢትዮጵያን መብትና ጥቅም ማስከበር የሚያስችሉ የዲጂታል ዲፕሎማሲ ዘመቻዎችን ማካሄዱን፣ የተቃውሞ ደብዳቤዎችን ለሚመለከታቸው ተቋማት መጻፉን፣ ሰልፎችንና የበይነ መረብ ውይይትችን ማካሄዱን ጠቅሰዋል፡፡

ከሃብት ማሰባሰብ አንጻርም ለልዩ ልዩ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችና ጥሪዎች ከፍተኛ ሀብት እንዲሰባሰብ ማድረጋቸውንም አንስተው፤ በተለይም ታላቁ ጉዞ ወደ ሀገር ቤት ጥሪን ተከትሎ ወደ ሀገር ቤት በመምጣት የተፈናቀሉ ወገኖችን መደገፍ የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸዋል፡፡

የዲፌንድ ኢትዮጵያን የአውሮፓ ግብረሀይል አንደኛ ዓመት ለማክበር በተዘጋጀው የበይነ መረብ መድረክ ላይ ተቋሙ የሚንቀሳቀስባቸው ሀገራትን የሚወክሉ የኤፌዲሪ አምባሳደሮችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶችም ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በልዩ ልዩ የአውሮፓ ሀገራት የዲፌንድ ኢትዮጵያ ተወካዮችም ያከናወኗቸው ዋና ዋና ተግባራትን ያቀረቡ ሲሆን፣ ስራቸውን አጠናክሮ ከመስራት አንጻር ሊደረጉ ይገባል ያሏቸውን ጉዳዮችም መነሳታቸውን በለንደን የኢትዮጰያ ኤምባሲ የተገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Source: Addis Meia Network-AMN