Concerning incidents on the Adwa Victory Day celebration

Download PDF and email the letter to your friends and networks

አማርኛ | English | Français | Czech | Español | italiano

የካቲት ፳፰ ቀን ፳፻ ፲፭ ዓ.ም

ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስተር ጽ/ቤት 

ለአዲስ አበባ መስተዳድር

ጉዳዩ፡ የአድዋ ድል በዓል አከባበር ችግሮችን በተመለከተ

የዲፌንድ ኢትዮጵያ ስቲሪንግ ግሩፕ በአዉሮፓ ባደረግነዉ ስብሰባ ከአድዋ በአል ጋር በተገናገኘ የመንግስት እና የግል ሚዲያ እንዲሁም በርካታ አካላት ያወጡትን መግለጫ እና በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጩ በርካታ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለመዳሰስ ሞክረናል።

እንደሚታወቀው መላው የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ግዛት በተያዙበት ዘመን፣ አውሮፓውያን አፍሪካን ለመቀራመት ተስማምተው በወራሪው የጣልያን መንግሥት አማካኝነት ሀገራችን ኢትዮጵያን በወረሩበት ጊዜ የንጉሱን የክተት አዋጅ ተከትሎ ሕዝቡ ለነፃነቱ በነቂስ ወጥቶ የጦር ግንባር ድረስ በመዝመት በዓድዋ ጦርነት ኢትዮጵያ ሀገራችን ድል እንድትቀዳጅና ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም የነፃነት አርማ እንድትሆን ማድረጉ  አኩሪ የጋራ ታሪካችን መሆኑ እሙን ነው፡፡ በተጨማሪም የአድዋ ድል ሃገራችን ካሏት ዋና ዋና  የመተሳሰሪያ አዕማዶቻችን ውስጥ አንዱ ነው። 

“ በብዙ ነገሮች ላንተሳሰር እንችላለን፤ ዐድዋ ገመድ ሆኖ ያስተሳስረናል። በብዙ ጉዳዮች ላንመሳሰል እንችላለን፤ ዐድዋ ቀለምና ቅርጽ ሰጥቶ ያመሳስለናል። በብዙ ነገሮች ላንግባባ እንችላለን፤ ቅድመ አያቶቻችንን አግባብቶ በአንድ አውድማ ያጋደለ “የዐድዋ ድል” ያግባባናል።”

በማለት ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ለበዓሉ ባስተላለፉት መልዕክት ገልፀውታል። 

ይሁን እንጂ ባለፉት ጥቂት ዓመታት አድዋ የአንድነት እና የኩራት  ታሪካችን መሆኑ ቀርቶ የልዩነት እና የክፍፍል ታሪክ እየሆነ መምጣቱ አብዛኛውን ሃገር ወዳድ በሃገር ውስጥ ያሉትን ዜጎች እና የዲያስፖራውን ማህበረሰብ የሚያሳስብ ሆኗል፡፡ 

በተለይም የዘንድሮው የአድዋ በዓል አከባበር ላይ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ሰብከት በተሰጡ መግለጫዎች መሰረት፣  በህፃናት እና አረጋውያን ላይ ጭምር የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት ያልተመጣጠነ እርምጃ በርካታ ሰዎች የአካል ጉዳት ሲደርስባቸው ቢያንስ አንድ ሰው መሞቱን ማረጋገጥ ችለናል።

ባንጻሩ፣ በመንግስት የተሰጡት መግለጫዎች የተድበሰበሱ ሲሆኑ በመደበኛ እና ማህበራዊ ሚዲያዎች ከተላለፉት የቀጥታ ስርጭት ተንቀሳቃሽ ምስሎች አንጻር ጉዳዩን በአግባቡ ለማስረዳት ያልቻሉ ሆነው አግኝተናቸዋል። ይህ አካሄድ በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሃገር ድጋፍ የሚያደርገውን ማህበረሰብ ሞራል የሚሰብር እምነቱንም የሚሸረሽር ሆኖ አግኝተነዋል።

ስለዚህ የዲፌንድ ኢትዮጵያ ስቲሪንግ ግሩፕ በአዉሮፓ የሚከተሉትን ምክረ ሃሳቦች ያቀርባል፤

  • በድርጊቱ ላይ የተሳተፉ የፀጥታ ኃይሎች ተለይተው ተመጣጣኝ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ይህንንም ሂደት የመንግስት ኮምኒኬሽን ከሚዲያ አካላት ጋር በመሆን ለማህበረሰቡ እንዲያስታውቅ።
  • በቀጣይ ጊዜያት ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይፈፀም የፀጥታ ኃይሎች ተገቢውን ስልጠና እንዲያገኙ ።
  • በዚህ ሂደት ለተጎዱት ወገኖቻችን አስፈላጊውን የሞራል እና የቁስ ካሳ እንዲደረግላቸዉ 
  • ከዚህ ድርጊት ጋር ከህግ አግባብ ውጭ የተያዙ እንዲለቀቁ።

በመጨረሻም፤ የበአሉን አከባበር በተመለከተ መንግስት ጉዳዩን ከማህበረሰብ ድርጅቶች፣ ከአርበኞች ማህበር ፣ ከከተማውን የጸጥታ ተቋማት እና ከከተማው አስተዳደር ያማከለ፣ የበዓሉን ታሪካዊ እና ባህላዊ ዳራ በጠበቀ መልኩ ሚከበርበትን መንገድ እንዲያመቻች እንጠይቃለን።

በትህትና፣ በአክብሮት እና በኃላፊነት ስሜት

The Steering Group of the Defend Ethiopia Task Force in Europe