የእምነት ተቋማትና የሕግ የበላይነት በኢትዮጵያ ትኩረት እንዲሰጣቸው ስለ መጠየቅ!

defend ethiopia task force in europe DETF EU

Download PDF and email the letter to your friends and networks
English አማርኛ | Français | Español | italiano         ግንቦት 27 2015 ዓ ም

ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስተር ጽ/ቤት አዲስ አበባ

ጉዳዩ፡ የእምነት ተቋማትና የሕግ የበላይነት በኢትዮጵያ ትኩረት እንዲሰጣቸው ስለ መጠየቅ!

ከላይ በርዕሱ ለመጥቀስ እነደሞከርነው እኛ በአውሮፓ የምንገኝ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሀገራችን የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በኢትዮጵያ ሀገራችን ላይ ተደቅኖ የነበረውን የምዕራቡን ዓለም ጫና እና ሃገርን የማፍረስ ዘመቻ በአንድነት ተሰባስበን በተለይም (Defend Ethiopia Task Force in Europe) በሚል የእንቅስቃሴ ስያሜ እስከዛሬይቷ ቀን ድረስ የሃይማኖት ፣ የዘር ፣ የጾታ ፣ የእውቀት እና የምንኖርበት የጂኦግራፊ ሁኔታ ሳያግደን በቻልነው ሁሉ ለኢትዮጵያ ሀገራችን ጋሻ ሆነን እንገኛለን። በመሆኑም አሁን በኢትዮጵያ በእምነት ተቋማትና የሕግ የበላይነት የማስከበር ሂደት የተነሳው ውዝግብ እጅጉን እያሳሰበን እና እያስጨነቀን ይገኛል።

የእምነት ተቋማት በኢትዮጵያ ከሃይማኖታዊ አገልግሎት በተጨማሪ ለሃገር ሰላም ግንባታ እና እድገት ያላቸውን ወሳኝ ሚና ከግምት በማስገባት በምእመናን ዙሪያ እየተከሰተ ያለው ሁኔታ ያሳሰበን ስለሆነ በቤተእምነቶች ወቅታዊ ችግር የህግ የበላይነት አለመከበር እና የጸጥታ ሃይሎች ያልተገባ ጣልቃ ገብነት ዙሪያ: የክልል እና የፌዴራል መንግስት አካላት ሃላፊነት በተሞላበት መንገድ ከወገንተኝነት የጸዳ ሚና አንዲጫወቱ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

ለዚህም ማሳያ ይሆን ዘንድ ሰሞኑን በሸገር ከተማ ፕሮጀክት ግንባታ ሂደት ወቅት በፈረሱ መስጊዶች ምክንያት እና እሱንም ተከትሎ ቤተ እምነታችንን አትንኩብን ብለው የዘወትር አርብ (ጁማአ) ፀሎታቸውን ለመከወን እና በዛውም የቤተ እምነታቸውን ፈረሳ በመቃወም ድምፃቸውን በማሰማት በነበሩት ንፁሀን ዜጎች ላይ የመንግስት የፀጥታ ሀይሎች የወሰዱት የዜጎችን ህይወት እስከመቅጠፍ የደረሰ ያልተገባ እርምጃ ተጠቃሾች ናቸው። በመሆኑም መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳታፊ በመሆን ለዜጎች እንግልት እና ሞት ምክንያት የሆኑትን ግለሰቦች ፣ ባልስልጣናትም ጭምር አጣርቶ ለህግ እንዲያቀርብልን እንዲሁም ህዝብ እንዲያውቀው እና የፖሊቲካዊ መረጋገትን ያመጣ ዘንድ ጉዳዩን ግልፅ በማድረግ በሚዲያ ገለጻዎች እንዲሰጡ በትህትና እንጠይቃለን::

በተጨማሪም በመንግስት በኩል የተከፈተውን ቀዳዳ እና የመረጃ ክፍተት በመጠቀም የሙስሊሙን ሰላማዊ ጥያቄ ተገን በማድረግ እና የፓለቲካ ትርፍ እናገኛለን ብለው በማሰብ መፍትሄ በማያመጣ አቅጣጫ እየተጓዙ ነገሮችን ወዳልተፈለገ ግጭትና ሁከት ለመውሰድ ስራን እየሰሩ ላሉ ግለሰቦች የማህበረሰብ አንቂዎች ማህበራት እና ጋዜጠኞች ጭምር ይህ አጋጣሚ በር የከፈተላቸው መሆኑን መንግስት ተረድቶ እነዚህን ክፍተቶች ባለመፍጠር እና የዜጎችን መብት በማክበር የህግ የበላይነትን እንዲያስከብር እንጠይቃለን።

ያለችን አንዲት ኢትዮጵያ ናት የምንለፋላት እድገቷን እና ብልጽግናዋን ዘወትር ማለዳ ከእንቅልፋችን ስንነቃ ለማየት እና ለመስማት የምንጓጓላት በመሆኑ የሚታየው ገራሚ ለውጥ ይበል የሚያስብል ቢሆንም በተቃራኒው ደግሞ ቀን ተቀን የዘር ፖለቲካው ፣ የኑሮው ውድነት: በተለይም የንፁሀን ዜጎች በተለያየ ምክንያት ሞት እና ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቅለው በየመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ሆነው ለችግር መዳረጋቸውን እያየን እና እያሰማን ልባችን እያዘነ ነው።  መንግስት ከህዝብ ጋር በመወያየት እና  በማስተባበር መፍትሄ ይሰጥ ዘንድ እንጠይቃለን:: 

እንደ ሃገር የተጋረጠብንን ችግር እና ኢትዮጵያችን እንደ ሀገር እንድትቀጥል በቅንነት እና በልበ ሰፊነት ህዝብን እና መንግስትን። የሚያራርቅ ሳይሆን የሚያቀራርብ ጉዳዮች ላይ ሀገራችንን የመጠበቅ ሀላፊነት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሀላፊነት ነው። ከህዝብ ፣ ከሀይማኖት አባቶች ፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና አባ ገዳዎች ጋር በመወያየት ችግሮቻችን በጥበብ እና በብልሃት ለመፍታት ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣትና ሀገሪቱን ለማረጋጋት የተቻላችሁን ሁሉ እንድታደርጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

ከታላቅ አክብሮት ጋር 

ሠላም ለኢትዮጵያ

ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ይባርክ

letter footer eu